አዋጅ ቁጥር ፱፻፳፫/፪ሺ፰


የኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት የወጣ አዋጅ

መሥራት ለሚችሉ ዜጎች ሁሉ በአገር ውስጥ ምቹ የሥራ ዕድሎች የሚስፋፉበትን ሁኔታ ለመፍጠር መንግሥት የሚያደርገው ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ ወደ ውጭ አገር በመሄድ ለመሥራት ፍላጎት ያላቸው ኢትዮጵያዊያን መብታቸው፣ ደህንነታቸው እና ክብራቸው ተጠብቆ ባላቸው ችሎታና አቅም ሠርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል አስፈላጊ በመሆኑ፤

ከተቀባይ አገሮች ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት መፈራረም ሕጋዊ የውጭ አገር ሥራ ስምሪትን በማጠናከር ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ጠቃሚ መሆኑ በመታመኑ፤

የግሉ ዘርፍ በውጭ አገር ሥራ ስምሪት አገልግሎት አሰጣጥ ሊኖረው የሚገባውን ተሳትፎ በሕግ መወሰን በማስፈለጉ፤

መንግሥት በውጭ አገር ሥራ ስምሪት አፈጻጸም የሚኖረውን የክትትልና የቁጥጥር ሚና ከፍ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤

በሥራ ላይ የነበረውን የሥራና ሠራተኛ ማገናኘት አገልግሎት አዋጅ በአዲስ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት ሕግ መተካት አስፈላጊ በመሆኑ፤ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ፶፭ (፩) መሠረት የሚከተለው ታውጇል፡፡

ክፍል አንድ

ጠቅላላ

፩. አጭር ርዕስ

ይህ አዋጅ “የኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር ፱፻፳፫/፪ሺ፰” ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

፪. ትርጓሜ

የቃሉ አገባብ ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ካልሆነ በስተቀር በዚህ አዋጅ ውስጥ ፦

፩/ “የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ” ወይም “ኤጀንሲ” ማለት መንግሥታዊ አካል ያልሆነና ከሠራተኛ ጋር የሥራ ውል ስምምነት በማድረግ ሠራተኛን በውጭ አገር ለሥራ ለአሠሪ የማቅረብ አገልግሎት የሚሰጥ ሰው ነው፤

፪/ “ፈቃድ” ማለት በሚኒስቴሩ ለኤጀንሲ የሚሰጥ በግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝነት ሥራ ላይ ለመሰማራት የሚያስችል የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ነው፤

፫/ “አሠሪ” ማለት አንድ ወይም ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎችን በዚህ አዋጅ በተመለከተው የሥራ ውል መሠረት በኤጀንሲ አማካኝነት፣ መንግሥት-ለመንግሥት በሚደረግ ስምምነት ወይም በዚህ አዋጅ በተደነገገው መሠረት በቀጥታ ቅጥር የሚያሰራ ሰው ነው፤

፬/ “ሠራተኛ” ማለት በዚህ አዋጅ በተመለከተው የሥራ ውል መሠረት ከአሠሪ ወይም ከኤጀንሲ ጋር በቅጥር ላይ የተመሠረተ የሥራ ግንኙነት ያለው ግለሰብ ሲሆን፣ እንደአግባቡ ሥራ ፈላጊንም ይጨምራል፤

፭/ “ቀጥታ ቅጥር” ማለት የመንግሥታዊ አካል ወይም የኤጀንሲ አገልግሎት ሳይሰጥ አሠሪውና ሠራተኛ በራሳቸው በሚያደርጉት ግንኙነት የሚፈፀም ቅጥር ነው፤

፮/ “የሥራ ሁኔታ” እና “የሥራ ላይ አደጋ” ማለት በአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ የተሰጣቸውን ትርጉም ይኖራቸዋል፤

፯/ “የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ማስረጃ” ማለት አንድ ሠራተኛ ለሚቀጠርበት ሥራ የመሥራት ብቃት ያለው ስለመሆኑ በሕግ ሥልጣን በተሰጠው አካል ተመዝኖ የሚሰጥ ማስረጃ ነው፤

፰/ “ቤተሰብ” ማለት የትዳር ጓደኛ፣ ወላጅ፣ ተወላጅ ወይም እስከ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ የሚቆጠር የሥጋ ወይም የጋብቻ ዘመድ ነው፤

፱/ “የሁለትዮሽ ስምምነት” ማለት የውጭ አገር የሥራ ቅጥር አስመልክቶ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክና በተቀባይ አገር መካከል የሚደረግ ስምምነት ነው፤

፲/ “ሚኒስቴር” ማለት የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው፤

፲፩/ “አግባብ ያለው ባለሥልጣን” ማለት በክልል የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ሕጎችን የማስፈጸም ኃላፊነት የተሰጠው አካል ነው፤

፲፪/ “ክልል” ማለት በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ፵፯(፩) የተመለከተው ማንኛውም ክልል ሲሆን የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ይጨምራል፤

፲፫/ “ሚሲዮን” ማለት በውጭ ሀገር የሚገኝ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቲክ ሚሲዮን፣ ቋሚ መልእክተኛ ጽሕፈት ቤት፣ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ወይም የንግድ ጽሕፈት ቤት ነው፤

፲፬/ “ንግድ ማህበር” ማለት የሽርክና ማህበር፣ የአክሲዮን ማህበር ወይም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ነው፤

፲፭/ “ሰው” ማለት ማንኛውም የተፈጥሮ ሰው ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ነው፤

፲፮/ በወንድ ጾታ የተገለጸው ማንኛውም አገላለፅ ሴትንም ይጨምራል፡፡

፫. የተፈጻሚነት ወሰን

ይህ አዋጅ ፦

፩/ በመንግሥታዊ አካል፣ በኤጀንሲ አማካኝነት ወይም በቀጥታ በሚደረግ ቅጥር የኢትዮጵያዊያን የውጭ አገር ሥራ ስምሪት ግንኙነት ላይ፣

፪/ ለትርፍ በሚካሄድ ሥራ ላይ ላልተመሠረተ ለቤት ሠራተኛነት ለመቀጠር ወደ ውጭ አገር በሚሄድ ኢትዮጵያዊ ላይ፣ ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡

ክፍል ሁለት

በመንግሥት ስለሚሰጥ የሥራ ስምሪት አገልግሎት

ንዑስ ክፍል አንድ

ስለሥራ ስምሪት አገልግሎት

፬. የሠራተኛ ምልመላና ስምሪት አገልግሎት

ሚኒስቴሩ መንግሥት ለመንግሥት በሚደረግ ስምምነት መሠረት በተቀባይ አገር ለሚገኝ መንግሥታዊ ድርጅት የሠራተኛ ምልመላና ስምሪት አገልግሎቶችን ሊሰጥ ይችላል፡፡

፭. ስለአገልግሎት ዓይነቶች

በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፬ መሠረት በሚኒስቴሩ የሚሰጡ የሠራተኛ ምልመላና ስምሪት አገልግሎቶች ቃለ መጠይቅና መረጣ ማድረግን፣ የጤና ምርመራ እንዲከናወን ማድረግን፣ የሥራ ውል ማፅደቅን፣ የቅድመ-ቅጥር እና ቅድመ-ጉዞ ገለፃ መስጠትን፣ የተቀጣሪ ሠራተኛ የውጭ ጉዞ ማመቻቸትን እና የመሳሰሉትን ሌሎች አገልግሎቶች ይጨምራል፡፡

፮. ቀጥታ ቅጥር የተከለከለ ስለመሆኑ

፩/ ማንኛውም አሠሪ በሚኒስቴሩ ወይም በኤጀንሲ በኩል ካልሆነ በስተቀር በቀጥታ ሠራተኛን መልምሎ ሊቀጥር አይችልም፡፡

፪/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) የተደነገገው ቢኖርም ሚኒስቴሩ በሚከተሉት ሁኔታዎች ቀጥታ ቅጥር ሊፈቅድ ይችላል፦

ሀ) አሠሪው የኢትዮጵያ ሚሲዮን አባል ከሆነ፤

ለ) አሠሪው ዓለም አቀፍ ድርጅት ከሆነ፤ ወይም

ሐ) ከየቤት ሰራተኛነት ቅጥር በስተቀር ማንኛውም ሥራ ፈላጊ በራሱ ጥረት
   የሥራ ዕድል ሲያገኝ፡፡

፫/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፪) (ሐ) መሠረት በቀጥታ የሚደረግ ቅጥር በሚኒስቴሩ ሊፈቀድ የሚችለው ፦

ሀ) ሠራተኛው በሚሄድበት አገር መብቱ፣ ደህንነቱና ክብሩ ሊጠበቅ እንደሚችል
   በሚመለከተው ሚሲዮን ወይም በተቀባዩ አገር ሚሲዮን ከሌለ አዲስ አበባ
   በሚገኘው የተቀባዩ አገር ሚሲዮን እና በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ
   ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተረጋገጠ፣

ለ) በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፷፪ (፩) መሠረት የተገባ የሕይወትና የአካል ጉዳት ካሣ
   ኢንሹራንስ ሽፋን ስለመኖሩ፣ እና

ሐ) ከሥራ ውሉ ጋር ምቹ የሆነ የአየር ወይም የየብስ መጓጓዣ አገልግሎት የሚያገኝ
   ስለመሆኑ፣ ማስረጃ ሲቀርብ ብቻ ነው፡፡

፬/ በዚህ አንቀጽ መሠረት ቀጥታ ቅጥር እንዲፈፅም ለተፈቀደ ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ ሊወጣ የሚችለው በሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ባለው ባለሥልጣን በኩል ብቻ ነው፡፡

ንዑስ ክፍል ሁለት

ትምህርት፣ ሥልጠና እና የጤና ምርመራ

፯. ስለ ትምህርት ደረጃና የሙያ ብቃት ምዘና

፩/ ለሥራ ወደ ውጭ አገር የሚሄድ ማንኛውም ሠራተኛ ፦

ሀ) ቢያንስ የስምንተኛ ክፍል ትምህርት ያጠናቀቀ፣ እና

ለ) በሚቀጠርበት የሥራ መስክ አግባብ ካለው የምዘና ማዕከል የሙያ ብቃት ማረጋገጫ
   ማስረጃ የያዘ፣ መሆን አለበት፡፡

፪/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት ሠራተኛው የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ማስረጃ እንዲያቀርብ የሚጠየቀው አሠሪው የሚጠይቃ ቸውን ሌሎች መስፈርቶች ማሟላቱ ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡

፰. ስለ ግንዛቤ ማሳደጊያ ፕሮግራም

ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን ፦

፩/ ለሥራ ወደ ውጭ አገር ለመሄድ ፍላጎት ላላቸው ዜጎች ስለተቀባይ አገር ሁኔታ፣ በሚሰማሩበት የሥራ መስክ ሊኖራቸው ስለሚገባ ክህሎት፣ ስለመብታቸውና ኃላፊነታቸው እና ስለመሳሰሉት ጉዳዮች የቅድመ-ስምሪትና የቅድመ-ጉዞ ግንዛቤ ማሳደጊያ ሥልጠና በመደበኛነት ይሰጣል፤

፪/ ሕብረተሰቡ ስለውጭ አገር ሥራ ስምሪት ተጨባጭ ሁኔታ ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃ እንዲያገኝ የመገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም ቀጣይነት ያለው አገር አቀፍ የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራዎችን ያከናውናል፤

፫/ ለኤጀንሲ የቦርድ አመራሮች፣ ሥራ አሥኪያጆች እና ሠራተኞች ስለውጭ አገር ሥራ ስምሪት ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማሳደጊያ ፕሮግራ ሞችን ያካሂዳል፤

፬/ ስለ ኢትዮጵያዊያን ሠራተኞች ምልመላና ቅጥር ሁኔታ፣ ስለውጭ አገር ሥራ ስምሪት በሥራ ላይ ስላሉ ሕጎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎች፣ ቅድመ ሁኔታዎች እና የተለያዩ መስፈርቶች ለውጭ አገር አሠሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለፃ ይሰጣል፡፡

፱. ስለ ጤና ምርመራ

፩/ የሠራተኛ የጤና ምርመራ የሚደረገው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሚመርጠው የጤና ተቋም ብቻ ይሆናል፡፡

፪/ ኤጀንሲው ሠራተኛን ለጤና ምርመራ መላክ ያለበት አሠሪው የሚጠይቃቸውን ሌሎች መስፈርቶች ማሟላቱ ሲረጋገጥ ብቻ ይሆናል፡፡

፫/ ሠራተኛው ከአንድ ጊዜ በላይ የጤና ምርመራ እንዲያደርግ የሚጠየቅ ከሆነ ወጪውን ኤጀንሲው መሸፈን ይኖርበታል፡፡

ንዑስ ክፍል ሦስት

ስለወጪ አሸፋፈንና የአገልግሎት ክፍያ

፲. ስለ ወጪ አሸፋፈን

፩/ የሚከተሉት ወጪዎች በአሠሪው ይሸፈናሉ፦

ሀ) የተቀባይ አገር የመግቢያ ቪዛ ክፍያ፤

ለ) የደርሶ መልስ የመጓጓዣ ክፍያ፤

ሐ) የሥራ ፈቃድ ክፍያ፤

መ) የመኖሪያ ፈቃድ ክፍያ፤

ሠ) የመድህን ዋስትና ሽፋን፤

ረ) በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኝ ለተቀባይ አገር ኤምባሲ ወይም ቆንስላ ጽሕፈት ቤት
   የሚከፈል ከቪዛና ከሰነድ ማረጋገጥ ጋር የተያያዘ ማንኛውንም ወጪ፤ እና

ሰ) የሥራ ውል ማፅደቂያ የአገልግሎት ክፍያ፡፡

፪/ የሚከተሉት ወጪዎች በሠራተኛው ይሸፈናሉ፦

ሀ) የፓስፖርት ማውጫ ወጪ፤

ለ) ከውጭ አገር የሚላክ የሥራ ቅጥር ውል ሰነድ እና ከወንጀል ነፃ ማስረጃ ማረጋገጫወጪ፤

ሐ) የሕክምና ምርመራ ወጪ፤

መ) የክትባት ወጪ፤

ሠ) የልደት ሰርተፊኬት ማውጫ ወጪ፤ እና

ረ) የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ማስረጃ ወጪ፡፡

፫/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፪) የተመለከቱ ወጪዎችን ሠራተኛው አውጥቶ በራሱ ጉድለት ባልሆነ ምክንያት በሥራ ላይ ካልተሰማራ ኤጀንሲው ወይም አሰሪው የሠራተኛውን ወጪ የመተካት ግዴታ ይኖርበታል፡፡

፬/ ለሥራ ወደ ውጭ አገር ለመሄድ አስፈላጊ ሁኔታዎች ተጠናቀው ያለበቂ ምክንያት ሠራተኛው ወደ ሥራው ባይሰማራ ከቅጥሩ ጋር በተያያዘ አሰሪው በዚህ አንቀጽ በንዑስ አንቀጽ (፩) ያወጣውን ወጪ ሠራተኛው እንዲከፍለው ሊጠይቅ ይችላል፡፡

፲፩. ስለ አገልግሎት ክፍያ

ሚኒስቴሩ አሠሪውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ መሠረት የሥራ ውል ማፅደቂያ የአገልግሎት ዋጋ ክፍያ ያስከፍላል፡፡

ንዑስ ክፍል አራት

ስለሁለትዮሽ ስምምነት እና አደረጃጀት

፲፪. የሁለትዮሽ ስምምነት ስለማስፈለጉ

በዚህ አዋጅ መሠረት ሠራተኛን በውጭ አገር ለሥራ ማሰማራት የሚቻለው በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በተቀባይ አገር መካከል የሁለትዮሽ ስምምነት ሲኖር ብቻ ነው፡፡

፲፫. ስለአደረጃጀት

፩/ ሚኒስቴሩ በዚህ አዋጅ የተሰጡትን ተግባሮች ለማከናወን አስፈላጊውን አደረጃጀት ይፈጥራል::

፪/ አግባብ ያለው ባለሥልጣን በዚህ አዋጅ የተሰጡትን ተግባሮች በክልል ደረጃ ለማከናወን አስፈላጊውን አደረጃጀት ይፈጥራል፡፡

፲፬. ሌበር አታሼ ስለመመደብ

፩/ ሚኒስቴሩ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመመካከርና መንግሥትን በማስፈቀድ በውጭ አገር ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎች መብት፣ ደህንነት እና ክብር እንዲጠበቅ ሌበር አታሼ በተቀባይ አገር በሚገኘው ሚሲዮን እንዲመደብ ያደርጋል፡፡

፪/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት የሚመደበው የሌበር አታሼ ተግባርና ኃላፊነት ሚኒስቴሩ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ በሚያወጡት የአሰራር መመሪያ ይወሰናል፡፡

፲፭. ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ እና ግብረ ኃይል

፩/ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር እና ስደተኞችን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር ፱፻፱/፪ሺ፯ አንቀፅ ፴፱ መሰረት የተቋቋመው ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ ፪ ላይ የተመለከቱትን ተግባራት ይፈፅማል።

፪/ በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ ፩ በተጠቀሰው አዋጅ መሰረት ለብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴው ተጠሪ የሆነው ግብረ ኃይል የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፦

ሀ/ ይህ አዋጅ በትክክል ሥራ ላይ መዋሉን ያረጋግጣል፤

ለ/ ለሥራ ወደ ውጭ አገር ሄደው በተለያዩ ምክንያቶች ወደ አገራቸው ለሚመለሱ
   ዜጎች የምክር አገልግሎት የሚሰጡና የመልሶ ማቋቋም ፕሮግራሞችን የሚያካሂዱ
   አካላት አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ ማግኘታቸውን ያረጋግጣል፤

ሐ/ ከሥራ ስምሪት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ከተቀባይ አገራት ጋር የሁለትዮሽ
   ስምምነት ሊደረግ ስለሚችልበት ሁኔታ እንዲጠናና አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠር ያደርጋል፤

መ/ በተቀባዩ አገር ውስጥ በዜጎች ላይ የመብት መጣስ ወይም ጉዳት ሲደርስ
   ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ለዚሁ ተጠያቂ በሆኑ ሰዎች ላይ ሕጋዊ
   እርምጃ መወሰዱን ያረጋግጣል፤

ሠ/ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር በሕገወጥ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ
   ድርጊት የሚሳተፉ ሰዎች በአፋጣኝ ሕግ ፊት ቀርበው መዳኘታቸውን ያረጋግጣል፤

ረ/ ሕገወጥ ሥራና ሠራተኛ የማገናኘት ድርጊትን በተመለከተ ለሕብረተሰቡ
   የግንዛቤ መፍጠሪያ ሥልጠና እንዲሰጥ ያደርጋል፤

ሰ/ የውጭ አገር ሥራ ስምሪትን በተመለከተ አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር የመረጃ
   ልውውጥ እንዲደረግና የተጠናከረ የመረጃ ማዕከል እንዲኖር ሁኔታዎችን ያመቻቻል፤

ሸ/ የራሱን የአሰራር መመሪያ ያወጣል፡፡

ክፍል ሦስት

ስለ ሥራ ሁኔታዎች

ንዑስ ክፍል አንድ

የሥራ ሁኔታዎችን ስለመወሰን

፲፮. ስለ ሥራ ሁኔታ

ሚኒስቴሩ ወቅታዊ የውጭ አገር የሥራ ገበያ ሁኔታዎችን እና ማህበራዊ አገልግሎቶችን አስመልክቶ የሥራ ሁኔታ መመሪያ ሊያወጣ ይችላል፡፡

፲፯. ስለ ሞዴል የሥራ ውል ይዘት

፩/ ሚኒስቴሩ ቢያንስ የሚከተሉትን ዝርዝሮች የያዘ ሞዴል የሥራ ውል ያዘጋጃል፦

ሀ) በተቀባይ አገር መነሻ ክፍያ ተብሎ ከተወሰነው፣ ኢትዮጵያና ተቀባይ
   አገር ባደረጉት የሠራተኛ ቅጥር ሁለትዮሽ ስምምነት መነሻ ክፍያ ተብሎ
   ከተደረሰው፣ ሁለቱ አገሮች ባፀደቁት ዓለም አቀፍ ስምምነት ከተመለከተው አነስተኛ
   የደመወዝ መጠን የማያንስ እና የተሻለ ጥቅም የሚሰጥ የደመወዝ፣መደበኛ የሥራ
   ስዓት እና የትርፍ ሰዓት ክፍያ፤

ለ) የዓመት፣ የሣምንት እና የመሳሰሉት ዕረፍቶች፤

ሐ) ወደ ሥራ ቦታ መሄጃና ከሥራ ቦታ መመለሻ ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት ወይም ተመጣጣኝ ክፍያ፤

መ) ነፃ ሕክምና፣ ምግብና መጠለያ ወይም ተመጣጣኝ ክፍያ፤

ሠ) የሕይወትና የአካል ጉዳት ዋስትና ሽፋን፤

ረ) የሥራ ውል የሚቋረጥባቸው በቂ ምክንያቶች፡፡

፪/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት ሞዴል የሥራ ውል ሲዘጋጅ በመሠረታዊነት የሚከተሉት መገናዘብ ይኖርባቸል፦

ሀ) የተቀባይ አገር ባህል፣ ልማድ፣ አኗኗር፣ የሠራተኛ እና የማህበራዊ ጉዳይ ሕጎች
   እንዲሁም የአሠሪ ድርጅት ፖሊሲዎች፤

ለ) ከተቀባይ አገር ጋር የተፈረሙ አግባብ ያላቸው የሁለትዮሽ እና የብዙ ወገን
   ስምምነቶች፣ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽኖች እና ውሳኔዎች፤

ሐ) የሥራ ገበያው ወቅታዊ ሁኔታዎች፡፡

፲፰. የተዋዋይ ወገኖች ነፃነት

ለሠራተኛ ይበልጥ የሚጠቅም እና የኢትዮጵያ የመንግሥት ፖሊሲ፣ ሕግንና የሕብረተሰቡን ሞራል የማይቃረን እስከሆነ ድረስ ተዋዋይ ወገኖች በሞዴል የሥራ ውል ያልተመለከቱ ሌሎች የሥራ ሁኔታዎችንና ጥቅሞችን በሥራ ውላቸው ውስጥ ሊያካትቱ ይችላሉ፡፡

፲፱. የማሳወቅ ግዴታ

፩/ ማንኛውም ኤጀንሲ ከሠራተኛ ምልመላና ቅጥር ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን መረጃዎች እና ስለሠራተኛው ሁኔታ የሚጠየቁ ሌሎች መረጃዎችን ሁሉ ለሚኒስቴሩ፣ አግባብ ላለው ባለሥልጣን ወይም ለሚሲዮኑ ተገቢ በሆነ ጊዜ ውስጥ ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡ ፪/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት መረጃዎች ሊቀርቡበት የሚገባውን ጊዜ ሚኒስቴሩ በመመሪያ ይወስናል፡፡

ንዑስ ክፍል ሁለት

ስለ ቁጥጥር አገልግሎት

፳. ስለ ቁጥጥር

፩/ ሚኒስቴሩ ለሥራ ወደ ውጭ አገር የሚሄዱ ሠራተኞችን ሕጋዊነት ለማረጋገጥ የሥራ ውል ለፀደቀላቸው ልዩ መታወቂያ ይሰጣል፡፡

፪/ ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን ማንኛውም ኤጀንሲ በዚህ አዋጅ መሠረት የተጣለበትን ግዴታና ኃላፊነት እየተወጣ ስለመሆኑ ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርግ የሥራ ሁኔታ ተቆጣጣሪ ይመድባል፡፡

፫/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፪) መሠረት የተመደበ ማንኛውም የሥራ ሁኔታ ተቆጣጣሪ የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባሮች ይኖሩታል፦


ሀ) ለኤጀንሲ የሥራ ፈቃድ ከመሰጠቱ ወይም ከመታደሱ ወይም ነባሩን የቢሮ
   አድራሻ ከመለወጡ በፊት የተሟላ ቢሮ፣ የምልመላ ሥርዓትና የቅድመ ቅጥር
   ገለፃና የምክር አገልግሎት መስጫ ቦታና ባለሙያ ማሟላቱን የማረጋገጥ፤

ለ) በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘመናዊ የመረጃ አያያዝና አጠቃቀም ሥርዓት የዘረጋ መሆኑን የማረጋገጥ

ሐ) በኤጀንሲ አማካይነት ወደ ውጭ አገር ለሥራ ተቀጥረው ለሚሄዱ ሠራተኞች
   ስለአጠቃላይ የሥራ ሁኔታና ስለሚሄዱ ባቸው አገሮች ሁኔታ መግለጫ እና
   የቅድመ-ቅጥርና ቅድመ-ጉዞ ትምህርትና ምክር አገልግሎት የተሰጠ መሆኑን የማረጋገጥ፤

መ) የዚህን አዋጅ ድንጋጌዎች ወይም በዚህ አዋጅ መሠረት የወጡ ደንቦችን ወይም
   መመሪያዎችን ኤጀንሲው መተላለፉን ራሱ ሲረዳ ወይም ጥቆማ ሲደርሰው
   ተገቢውን ማጣራት የማከናወን፤

ሠ) ሕገ ወጥ የሠራተኛ ምልመላና ቅጥር ተግባር እንዳይከናወን ቁጥጥር የማካሄድ፤

ረ) በኤጀንሲው ቢሮ በማንኛውም የሥራ ሰዓት በመገኘት አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶችን፣
   መዝገቦችን፣ የሂሳብ መዛግብቶችንና የመሳሰሉትን የመመርመርና ጥያቄ የማቅረብ ፡፡

፬/ የሥራ ሁኔታ ተቆጣጣሪው በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፫) መሠረት ቁጥጥር ሲያካሂድ ከሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ካለው ባለሥልጣን የተሰጠውን መታወቂያ ይዞ መገኘት እና ማሳየት አለበት፡፡

፭/ የሥራ ሁኔታ ተቆጣጣሪው በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፫) መሠረት ባካሄደው ቁጥጥር የደረሰበትን ግኝትና ሊወሰድ ስለሚገባው ሕጋዊ እርምጃ ከውሳኔ ሃሳብ ጋር ለሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ላለው ባለሥልጣን ማቅረብ አለበት፡፡

፮/ ሚኒስቴሩ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፫) መሠረት ቁጥጥር የሚካሄድበትን የአፈጻጸም ሥነ-ሥርዓት መመሪያ ሊያወጣ ይችላል፡፡

፯/ የሥራ ሁኔታ ተቆጣጣሪው ሥልጣኑን አለአግባብ በመጠቀም ለሚፈፅመው ድርጊት አግባብ ባለው ሕግ መሠረት ተጠያቂ ይሆናል፡፡

፰/ ለሥራ ሁኔታ ተቆጣጣሪ ተግባር መሳካት ማንኛውም ኤጀንሲ የመተባበር ግዴታ አለበት፡፡

ክፍል አራት

በኤጀንሲ ስለሚሰጥ የሥራ ስምሪት አገልግሎት

ንዑስ ክፍል አንድ

ስለፈቃድ፣ ለፈቃድ ብቁ ስለመሆንና ስላለመሆን

፳፩. ፈቃድ ስለማስፈለጉ

፩/ በዚህ አዋጅ መሠረት ኤጀንሲ ሆኖ ለመሥራት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ከሚኒስቴሩ ፈቃድ ማግኘት አለበት፡፡

፪/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት ፈቃድ በማውጣት ከአንድ አገር በላይ ለመሥራት የሚፈልግ ሰው ለእያንዳንዱ አገር ፈቃድ ማውጣት አለበት፡፡

፳፪. ፈቃድ ለማግኘት ብቁ ስለመሆን

ኤጀንሲ ሆኖ ፈቃድ ለማግኘት፦

፩/ አመልካቹ ግለሰብ ድርጅት ከሆነ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው እና ከአንድ ሚሊዮን ብር ያላነሰ ካፒታል ያለው፣

፪/ አመልካቹ የንግድ ማህበር ከሆነ የተቋቋመበት ዓላማ በውጭ አገር ሥራና ሠራተኛ የማገናኘት አገልግሎት ለመስጠት ብቻ የተቋቋመ፣ የንግድ ማህበሩ አባላት በሙሉ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸው እና ከአንድ ሚሊዮን ብር ያላነሰ የተዋጣ አክሲዮን ወይም መዋጮ ያለው፣

፫/ በዚህ አዋጅና በሌሎች ሕጎች መሠረት በውጭ አገር ሥራ ስምሪት ዘርፍ እንዳይሰማራ ያልተከለከለ፣ መሆን ይኖርበታል፡፡

፳፫. ፈቃድ ለማግኘት ብቁ ስላለመሆን

ከዚህ በታች የተመለከቱት ፈቃድ ለማግኘት ብቁ አይሆኑም፦

፩/ አዋጅ ቁጥር ፮፻፴፪/፪ሺ፩ ወይም አዋጁን ለማስፈጸም የወጣ ደንብ ወይም መመሪያ በመጣስ ፦

ሀ) ፈቃዱ የተሰረዘበት ማንኛውም ኤጀንሲ፣ አባሎቹ እና ኤጀንሲው የአክሲዮን
   ማህበር ከሆነ የማህበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት፤

ለ) የሠራተኞች መብት፣ ደህንነት እና ክብር በመጣሱ ምክንያት ለቀረቡ አቤቱታዎች
   መፍትሔ ባለመስጠቱ ፈቃዱ የተሰረዘበት፤

ሐ) ከሦስት ጊዜ በላይ ፈቃዱ የታገደበት ወይም የፈቃድ ስረዛ ቅድመ
   ማስጠንቀቂያ በጽሁፍ የተሰጠው ማንኛውም ኤጀንሲና አባሎቹ፤

፪/ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ስደተኞችን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር በተደራጁ ወንጀሎች፣ በሽብርተኝነት በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ወይም በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀል ተከሶ በፍርድ ቤት የተቀጣ ሰው ወይም በወንጀል ድርጊቱ ተከሶ ጉዳዩ በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ያለ ሰው ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ፤

፫/ የጉዞ ወኪል እና የአየር መንገድ ቲኬት ሽያጭ ቢሮ ወይም የወኪሉ ወይም የቢሮው ሠራተኛ፣ ትራንዚተር ወይም መርከበኛ፤

፬/ የሚኒስቴሩ፣ አግባብ ያለው ባለሥልጣን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ፣ የፖሊስ ኮሚሽን ወይም ይህን አዋጅ በቀጥታ የሚያስፈጽም የመንግሥት አካል ማንኛውም የሥራ ኃላፊ፣ ሠራተኛ ወይም በውጭ አገር የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ አመራር አባል እና የእነዚሁ ቤተሰቦች፡፡

ንዑስ ክፍል ሁለት

ስለፈቃድ አሰጣጥ

፳፬. ፈቃድ ለማግኘት መሟላት ስላለባቸው መሥፈርቶች

በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፳፪ መሠረት ብቁ የሆነ ማንኛውም አመልካች ፈቃድ ለማግኘት ለዚሁ የተዘጋጀውን የማመልከቻ ቅጽ በመሙላት ከሚከተሉት ሰነዶች ጋር አሟልቶ ማቅረብ ይኖርበታል፦

፩/ በኤጀንሲነት ሥራ ለመሰማራት የሚያስችለው የንግድ ምዝገባ እና የንግድ ስያሜ የምስክር ወረቀት፤

፪/ አመልካቹ ሥራውን የሚያካሂደው በንግድ ማህበርነት ከሆነ በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽሕፈት ቤት የተረጋገጠ የመመሥረቻ ጽሁፍና የመተዳደሪያ ደንብ ዋና ቅጂ፤

፫/ አመልካች ፈቃድ ለማውጣት የጠየቀው በግል ከሆነ ግለሰቡ፣ በሽርክና ማህበርነት ከሆነ የማህበሩ አባላት ወይም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ወይም በአክሲዮን ማኅበር ከሆነ የዳይሬክተሮች ቦርድ እና አመራር አካላት እንዲሁም የሥራ ኃላፊዎችና ተቀጣሪ ሠራተኞች በዚህ አዋጅ በአንቀጽ ፳፫(፪) ከተመለከቱ ወንጀሎች ነፃ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ከፖሊስ የተሰጠ ማስረጃ፤

፬/ የአደረጃጀት መዋቅሩን የሚያሳይ ቻርት፣ ለሥራ የሚያስፈልግ የሰው ኃይል ዝርዝርና የትምህርት ማስረጃ፣ የእያንዳንዱ ኃላፊና ሠራተኛ የሥራ መደብ፣ የግል ታሪክ፣ የፓስፖርት መጠን ያላቸው ሁለት ጉርድ ፎቶግራፎች፤

፭/ የአመልካቹ የሥራ ቦታ አድራሻና የቢሮው ይዞታ የራስ ከሆነ የባለቤትነት ማረጋገጫ ደብተር ወይም ኪራይ ከሆነ የኪራይ ውል በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽሕፈት ቤት የተረጋገጠ ዋና ቅጂ፤

፮/ በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፷(፩) የተመለከተውን የዋስትና ግዴታ ማሟላቱን የሚገልፅ ማረጋገጫ ሰነድ፤

፯/ ሥራ አስኪያጁ ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ እና በሥራ አመራር ሦስት ዓመት የሥራ ልምድ ያለው ስለመሆኑ ማረጋገጫ ሰነድ፤

፰/ ሥራው የሚቋቋመው በግለሰብ ከሆነ ባለቤቱ እና ሥራ አስኪያጁ፣ በንግድ ማህበርነት ከሆነ የማኅበሩ አባላትና የአመራር አካላት በቅድመ ፈቃድ ሥልጠና ላይ ስለመሳተፋቸው የሚገልፅ የምስክር ወረቀት፣

፱/ ሠራተኛን በሚልክበት አገር ፦

ሀ) የተሟላ ቢሮ ስለመክፈቱ ወይም የተቀባይ አገር ዜግነት ያለውና በአገሩ አግባብ ባለው
   የመንግሥት አካል በሥራና ሠራተኛ አገናኝነት ሥራ ላይ ለመሳተፍ የሚያስችል
   ፈቃድ ያለውን ሰው በውክልና ስለመሰየሙ የተረጋገጠ ማስረጃ፤

ለ) በዚህ ንዑስ አንቀጽ ፊደል ተራ (ሀ) የተመለከተው ተወካይም ውክልናውን
   ስለመቀበሉ በሚመለከተው ሚሲዮን ወይም በተቀባዩ አገር ሚሲዮን ከሌለ
   አዲስ አበባ በሚገኘው የተቀባዩ አገር ሚሲዮን እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
   የተረጋገጠ ሰነድ ማስረጃ፣እና

ሐ) ለሠራተኛው ጊዜያዊ የምግብና የመጠለያ አገልግሎት መስጫ ቦታ ያዘጋጀ
   ስለመሆኑ በሚመለከተው ሚሲዮንና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተረጋገጠ ደብዳቤ፣

፲/አመልካቹ ሠራተኛ ወደሚልክበት አገር በነፃነት መግባትና መውጣት የሚችል ስለመሆኑ በሚመለከተው አካል የተሰጠ ማረጋገጫ፤

፲፩/ቀደም ሲል ፈቃድ ተሰጥቶት ሲሰራ በነበረበት ጊዜ የሚፈለግበትን ግብር የከፈለ ስለመሆኑ ማስረጃ፤

፲፪/ የፈቃድ ክፍያ መፈጸሙን የሚያሳይ ደረሰኝ፤

፲፫/ እንደ አስፈላጊነቱ ሚኒስቴሩ በመመሪያ የሚወስናቸው ሌሎች ማስረጃዎች፡፡

፳፭. ፈቃድ ስለመስጠት

ሚኒስቴሩ በዚህ አዋጅ መሠረት ፈቃድ ለማግኘት የሚያበቁ ሁኔታዎች መሟላታቸውን በማረጋገጥ በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ለአመልካቹ ፈቃድ ይሰጣል፤ የቀረበው የፈቃድ ጥያቄ ተቀባይነት የሌለው ከሆነም በዚሁ ጊዜ ውስጥ ለአመልካቹ በጽሁፍ ያስታውቃል፡፡

፳፮. ፈቃድ ፀንቶ ስለሚቆይበት ጊዜ

በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፳፭ መሠረት የተሰጠ ፈቃድ ለአንድ ዓመት የፀና ይሆናል፡፡

፳፯. ፈቃድን በግልፅ ቦታ ስለማስቀመጥ

ማንኛውም ኤጀንሲ በዚህ አዋጅ መሠረት የተሰጠውን ፈቃድ በከፈተው ቢሮ ውስጥ ግልፅ ሆኖ በሚታይ ቦታ ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡

፳፰. የሥራ ፈቃድ ማስተላለፍ እና ከአንድ ኤጀንሲ በላይ መሳተፍ የተከለከለ ስለመሆኑ

፩/ ማንኛውም ኤጀንሲ በሚኒስቴሩ የተሰጠውን ፈቃድ ለሌላ ሰው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ማስተላለፍ ክልክል ነው፡፡

፪/ ማንኛውም ሰው ከአንድ ኤጀንሲ በላይ ባለቤት፣ የሽርክና ወይም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አባል፣የቦርድ አመራር፣ሥራ አስኪያጅ ወይም ሠራተኛ ሆኖ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ መሥራት አይችልም፡፡

፫/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) የተመለከተው ቢኖርም ኤጀንሲው በግለሰብ የተቋቋመ ከሆነና ግለሰቡ ከሞተ ለሥራ ወደ ውጭ አገር የተላኩ ዜጎች መብት፣ ደህንነትና ክብር ለማስጠበቅ ሲባል ብቻ ሥራውን ላለማስተጓጎልና ለማጠና ቀቅ በግለሰቡ ሕጋዊ ወራሾች ጠያቂነት የሥራ ፈቃዱ ለነዚህ ወራሾች ሊተላለፍ ይችላል፡፡

፬/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፫) የተመለከቱት ወራሾች በዘላቂነት ሥራውን ማስቀጠል ከፈለጉ ሚኒስቴሩ ጠያቂዎቹ ለፈቃድ ብቁ መሆናቸውን በማረጋገጥ ፈቃዱን ሊያስተላልፍላቸው ይችላል፡፡

፳፱. የአመራር ወይም የሠራተኛ ለውጥ ስለማሳወቅ

ማንኛውም ኤጀንሲ የቦርድ አመራር ወይም የሥራ አስኪያጅ ለውጥ ሲያደርግ ወይም ሠራተኛን ሲቀጥር ወይም ሲያሰናብት ይህንኑ እንደአግባቡ ለሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ላለው ባለሥልጣን በ፲ የሥራ ቀናት ውስጥ ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡

፴. አመራርን ለሕዝብ ይፋ ስለማድረግ

ማንኛውም ኤጀንሲ በሥራ አስኪያጁ ወይም በዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ላይ ያደረገውን ለውጥ ሰፊ ሽፋን ባለው ጋዜጣ፣ሬዲዮና ቴሌቪዥን በሰባት የሥራ ቀናት ውስጥ ለሕዝብ ይፋ በማድረግ ይህንኑ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ለሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ላለው ባለሥልጣን ማቅረብ ይኖርበታል፡፡

፴፩. በአገር ውስጥ ተጨማሪ ቢሮ ስለመክፈት

ማንኛውም ኤጀንሲ ለሥራ ማካሄጃ በአገር ውስጥ ተጨማሪ ቢሮ መክፈት ሲፈልግ ከሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ካለው ባለሥልጣን ፈቃድ ማግኘት ይኖርበታል፡፡

፴፪. የቢሮ አድራሻ ለውጥ ስለማድረግና ስለማሳወቅ

ማንኛውም ኤጀንሲ ፦

፩/ የቢሮ አድራሻ ለውጥ ማድረግ የሚችለው ቢሮው በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፳፬(፭) የተመለከተው ማሟላቱን እንደአግባቡ ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን አረጋግጦ ሲፈቅድለት ብቻ ነው፤

፪/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት ተፈቅዶ የተፈፀመውን የቢሮ አድራሻ ለውጥ በሰባት የሥራ ቀናት ውስጥ ሰፊ ሽፋን ባለው ጋዜጣ ላይ ለሕዝብ በማሳወቅ ለሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ላለው ባለሥልጣን ማስረጃውን ማቅረብ አለበት፡፡

፴፫. ስለ ፈቃድ ዕድሳት

፩/ በዚህ አዋጅ መሠረት የሚሰጥ ፈቃድ በየዓመቱ የሚታደስ ይሆናል፡፡

፪/ ማንኛውም ኤጀንሲ ፈቃድ ለማደስ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) የተመለከተው የጊዜ ገደብ ከማለቁ በፊት ባለው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለዚሁ የተዘጋጀውን የማመልከቻ ቅጽ በመሙላት የሚከተሉትን ሰነዶች አሟልቶ ለሚኒስቴሩ ማቅረብ ይኖርበታል ፦

ሀ) በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፷ (፩) የተመለከተውን የዋስትና ግዴታ
   ማሟላቱን የሚያሳይ ማስረጃ፤

ለ) በውጭ ኦዲተር የተመረመረ የዘመኑ የሂሳብ ሪፖርትና ግብር የተከፈለ ስለ
   መሆኑ ማስረጃ፤

ሐ) በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፳፬(፫) የተዘረዘሩት አካላት በዚሁ አዋጅ በአንቀጽ ፳፫(፪)
   መሠረት ከወንጀል ነፃ ለመሆናቸው ከፖሊስ ማስረጃ፤

መ/ በተቀባይ አገር የተሰየመው ወኪል የታደሰ የንግድ ፈቃድ ማስረጃዎች፤

ሠ) ለሥራ ወደ ውጭ አገር ስላሰማራቸውና ስለተመለሱት ሰራተኞች የሚገልፅ አጠቃላይ ሪፖርት፤

ረ) በሚኒስቴሩ መመሪያ የተወሰኑ ሌሎች ማስረጃዎች፡፡

፫/ ሚኒስቴሩ በዚህ አዋጅ መሠረት ፈቃድ ለማደስ የሚያበቁ ሁኔታዎች መሟላታቸውን እንዳረጋገጠ የፈቃድ ዕድሳት ክፍያ እንዲፈጽም በማድረግ በሦስት የሥራ ቀናት ውስጥ ፈቃድ ያድሳል፤ የቀረበው የፈቃድ ዕድሳት ጥያቄ ተቀባይነት የሌለው ከሆነም በዚሁ ጊዜ ውስጥ ለአመልካቹ በጽሁፍ ያስታውቃል፡፡

፬/ በዚህ አዋጅ በአንቀጽ ፳፮ መሠረት ፀንቶ የሚቆይበት ጊዜ ሲጠናቀቅ ያልታደሰ የኤጀንሲ ፈቃድ ታግዶ ይቆያል፡፡

፭/ ኤጀንሲው ፈቃዱን በወቅቱ ሳያሳድስ የቀረ እንደሆነ ፀንቶ የሚቆይበት ጊዜ ካበቃበት በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ውስጥ ለመጀመ ሪያው ወር የዕድሳት ክፍያውን ሃያ በመቶ፣ ለሁለተኛው ወር አርባ በመቶ እና ለሦስተኛው ወር ስልሳ በመቶ ቅጣት በተጨማሪ በመክፈል ፈቃዱን ሊያሳድስ ይችላል፡፡

፴፬. ስለ ማበረታቻ ሥርዓት

ሚኒስቴሩ በዘርፉ የተሰማሩ ኤጀንሲዎችን አፈፃፀም በመገምገም የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡትን ለማበረታታት የማበረታቻ አሠጣጥ ሥርዓት መመሪያ ሊያወጣ ይችላል፡፡

ንዑስ ክፍል ሦስት

ስለ ሥራ ስምሪት አገልግሎት

፴፭. ስለውጭ አገር ሥራ ማስታወቂያ

፩/ ማንኛውም ኤጀንሲ ስለውጭ አገር ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ ከማውጣቱ በፊት እንደአግባቡ ለሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ላለው ባለሥልጣን በማቅረብ ማስመዝገብና ማፀደቅ ይኖርበታል፡፡

፪/ ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ በማናቸውም የመገናኛ ብዙኃን ሲወጣ የሚከተሉትን መያዝ ይኖርበታል፦

ሀ) የኤጀንሲውን ስም፣ አድራሻ፣ በሚኒስቴሩ የተሰጠውን ፈቃድ ቁጥር እና ሠራተኛ
   ለመላክ የተፈቀደለት አገር፤

ለ) ስለተገኘው ክፍት የሥራ መደብና ና ብዛት፣ተፈላጊ ችሎታ፣ የደመወዝ መጠን፣
   የቅጥር ቆይታ ጊዜ፣ሥራው የተገኘበት ፣ አገር፣ቦታ እና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎች፤

ሐ) ኤጀንሲው ለሚሰጠው ማንኛውም አገልግሎት ሰራተኛውን ምንም ዓይነት
   የአገልግሎት ክፍያ የማያስከፍል ስለመሆኑ መግለጫ፡፡

፴፮. ስለ ሠራተኛ ምልመላ

፩/ ማንኛውም ኤጀንሲ የሠራተኛ ምልመላ ማከናወን የሚችለው በከፈተው ቢሮ ውስጥ ብቻ መሆን አለበት፡፡

፪/ የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) ድንጋጌ ቢኖርም የሚፈጸመው የሠራተኛ ምልመላ ብዙ የሰው ኃይል የሚጠይቅ ከሆነ ጊዜያዊ ምልመላ የሚካሄድበትን ቦታ እንደአግባቡ ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን ሊፈቅድ ይችላል፤ ዝርዝር አፈፃፀሙ ሚኒስቴሩ በሚያወጣው መመሪያ ይወሰናል፡፡

፴፯. የሥራ ውልን ስለማፅደቅ

፩/ ማንኛውም ኤጀንሲ ሚኒስቴሩ ያወጣውን ሞዴል የሥራ ውል መሠረት በማድረግ አሠሪ፣ ኤጀንሲው እና ሠራተኛው የፈረሙበትን የሥራ ውል እና ሌሎች ሚኒስቴሩ በመመሪያ የወሰና ቸውን መሥፈርቶች በማሟላት እንዲፀድቅ ለሚኒስቴሩ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡

፪/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) በተጠቀሰው የሥራ ውል የተመለከተው የአሠሪ ፊርማና ሌሎች ተዛማጅ ሰነዶች ትክክለኛነት በሚመለ ከተው ሚሲዮን እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

፫/ ሚኒስቴሩ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) እና (፪) የተመለከቱት ሁኔታዎች መሟላታቸውን እንዳረጋገጠ በመመሪያ በሚወሰነው የጊዜ ገደብ ውስጥ የቀረበውን የሥራ ውል በማፅደቅ ይመዘግባል፡፡

፴፰. ሠራተኛን ለሥራ ስለማሰማራትና ስለማሳወቅ

ማንኛውም ኤጀንሲ ፦

፩/ የሥራ ውል በፀደቀ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሠራተኛን ለሥራ ማሰማራት፣

፪/ ወደ ውጭ አገር ለሥራ የላከውን ሠራተኛ በሚሄድበት አገር ላለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ወይም ቆንስላ ጽሕፈት ቤት በ፲፭ ቀናት ውስጥ አሳውቆ የማስመዝገብ፣ የሥራ ፈቃድና የመኖሪያ ፈቃድ ስለማግኘቱ የማረጋገጥና ይህንኑ መረጃ አሟልቶ ለሚኒስቴሩ ማቅረብ፣ ይኖርበታል፡፡

፴፱. የሥራ ውልን ስለማሰረዝ

በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፴፰(፩) በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ኤጀንሲው ሠራተኛን ወደ ሥራ ማሰማራት ካልቻለ የጸደቀው የሥራ ውል እንዲሰረዝ ከነምክንያቱ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለሚኒስቴሩ ማሳወቅ አለበት፡፡

፵. ስለ የጋራ እና የተናጠል ኃላፊነት

ከሠራተኛ ጋር የተደረገ የሥራ ውል ቢጣስ ኤጀንሲውና አሠሪው ለሠራተኛው መብት በጋራና በተናጠል ኃላፊ ይሆናሉ፡፡

ክፍል አምስት

ስለጥፋት እና ሊወሰድ ስለሚገባው እርምጃ

ንዑስ ክፍል አንድ

በኤጀንሲ ስለሚፈፀሙ ጥፋቶችና ስለሚወሰዱ እርምጃዎች

፵፩. አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የመወሰን ሥልጣን

ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን ኤጀንሲው ከሠራተኛ ያለአግባብ የተቀበለውን ገንዘብ የማስመለስ ጥያቄን ጨምሮ ይህን አዋጅና አዋጁን መሠረት አድርጎ የወጣ ደንብና መመሪያ በመጣሱ ምክንያት የሚነሱ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የመስማትና የመወሰን ሥልጣን ይኖረዋል፡፡

፵፪. የጥፋት ዓይነቶች

፩/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፪) ወይም (፫) ከተመለከቱት ጥፋቶች አንዱን በፈፀመ ኤጀንሲ ላይ የፈቃድ ዕገዳ ወይም ስረዛ እርምጃ ይወሰድበታል፡፡

፪/ የሚከተሉት የፈቃድ ዕገዳን የሚያስከትሉ ጥፋቶች ናቸው ፦


ሀ) ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን ቁጥጥር እንዲያካሂድ የመደበውን
   የሥራ ሁኔታ ተቆጣጣሪ ሥራ ማሰናከል ወይም ለማሰናከል መሞከር፤

ለ) ለሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ላለው ባለሥልጣን በቅድሚያ ሳያሳውቅ ሥራ
   አስኪያጅ ወይም የአመራር ቦርድ አባል መሾም ወይም ሠራተኛ መቅጠር፤

ሐ) ቢያንስ የስምንተኛ ክፍል ትምህርት ያላጠናቀቀ እና አግባብ ካለው የምዘና
   ማዕከል የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ማስረጃ ያልያዘን ሠራተኛ መመልመል፤

መ) በራሱ ኤጀንሲ የተመዘገበን ሠራተኛ ካልሆነ በስተቀር ማንኛውም አሰሪ ሰራተኛ
   እንዳይቀጥር ተፅዕኖ ማሳደር ወይም ተፅዕኖ ለማሳደር መሞከር፤

ሠ) ያለበቂ ምክንያት ሠራተኛን በሕጉ በተወሰነው ጊዜ ውስጥ ለሥራ ማሰማራት አለመቻል፤

ረ) የላካቸው ሠራተኞች መብት፣ ደህንነት እና ክብር በመጣሱ ምክንያት
   ለሚቀርበው አቤቱታ መፍትሄ አለመስጠት፤

ሰ) በሕግ አግባብ ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለስልጣን የሚሰጣቸውን
   ትዕዛዞችና ማስታወቂያዎች አለመፈጸም እና ሌሎች አሰራሮችን አለመከተል፤

ሸ) ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን የሚጠይቃቸውን ለሥራ
   የተሰማሩ ሠራተኞች ወቅታዊ ሪፖርቶች፣ የተገኙ ክፍት የሥራ ቦታዎች፣ በሥራው
   ምክንያት ከውጭ አገር በኮሚሽን መልክ ገቢ የተደረገለትን የውጭ አገር ምንዛሪ
   ገንዘብ መጠን በየወቅቱ አለማሳወቅ፤

ቀ) በተለያዩ ምክንያቶች ከሥራቸው የተለዩ ሠራተኞች ዝርዝር እና ሌሎች ተመሳሳይ
   መረጃዎችን በሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ባለው ባለሥልጣን የሚጠየቁ መረጃዎችን አለማቅረብ፤

በ) ፈቃዱን ሥራውን በሚያካሄድበት ቢሮ ውስጥ ግልጽ ሆኖ ሊታይ በሚችልበት ቦታ አለማኖር፤

ተ) በዚህ አዋጅ መሠረት መስጠት የሚገባውን አገልግሎት በተሟላ ሁኔታ አለመስጠት፤

ቸ) የሠራተኛውን ደመወዝ ወይም ሠራተኛው ወደ አገሩ የሚልከውን ገንዘብ መያዝ፤

ኀ) በራሱ ባልሆነ ምክንያት ወደ ሥራ ያልተሰማራ ሠራተኛ ያወጣውን ወጪ ያለመተካት፤

ነ) ለሠራተኞች የቅድመ-ጉዞ ገለፃ እና የምክር አገልግሎት አለመስጠት፤

ኘ) ሠራተኛው ለሥራ በሄደበት አገር የአካል ጉዳት ወይም የሞት አደጋ ሲደርስበት
   የአደጋውን መንስኤና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎችን ወዲያውኑ በማጣራት ለሚኒስቴሩ አለማሳወቅ፤

አ) በዚህአዋጅ በአንቀጽ ፷(፬) የተመለከተውን አለመፈጸም፡፡

፫/ የሚከተሉት የፈቃድ ስረዛን የሚያስከትሉ ጥፋቶች ናቸው ፦

ሀ) በግለሰብ የተቋቋመ ኤጀንሲ ወይም ባለቤቱ፣ ሥራ አስኪያጁ ወይም
   ሠራተኛው በጉዞ ወኪል ወይም የአየር መንገድ ቲኬት ቢሮ ውስጥ በአመራር
   ወይም በሠራተኛ ነት፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተሳታፊ ሆኖ መገኘት፤

ለ) ፈቃድ የተሰጠው ኤጀንሲ የተቋቋመው ፦

    (፩) በሽርክና ወይም ኃላፊነቱ በተወሰነ የግል ማህበር ከሆነ የማህበሩ
        አባላት፣ ሥራ አስኪያጁ ወይም ሠራተኛው፤
    (፪) በአክሲዮን ማህበር ከሆነ የማህበሩ የዳይሬክተሮች የቦርድ አባላቱ፣ ሥራ
        አስኪያጁ ወይም ሠራተኛው፤ በጉዞ ወኪል ወይም የአየር መንገድ
        ትኬት ቢሮ ውስጥ በአመራር ወይም በሠራተኛነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ
        መንገድ ተሳታፊ ሆኖ መገኘት

ሐ) በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፴፫(፭) መሠረት ፈቃድ በወቅቱ አለማሳደስ፤ መመልመልና ለሥራ ማሰማራት፤

ሠ) ፈቃድን በተሳሳተ መረጃ ማግኘት ወይም ማሳደስ፤

ረ) በኢትዮጵያ እና በተቀባይ አገር መካከል የሠራተኛ ቅጥር የሁለትዮሽ ስምምነት
   ከተፈፀመበት አገር ውጭ ወይም ሚኒስቴሩ ሠራተኛ ለሥራ እንዳይሰማራ
   ወደ ከለከለበት አገር ሠራተኛን ለመላክ መመልመል ወይም ማሰማራት፤

ሰ) የሕዝብን ጤና ወይም ሞራል በሚጎዳ ወይም የአገሪቷን ክብርና ገፅታ ለሚያጎ
   ድፍ ሥራ ሠራተኛን መመልመል ወይም ማሰማራት፤

ሸ) የተሰጠውን ፈቃድ በዚህ አዋጅ ከተመለ ከተው ውጭ ለሌላ ማስተላለፍ ወይም
   ባለቤትነትን መቀየር፤

ቀ) የሥራ ስምሪት አገልግሎትን ምክንያት በማድረግ ከሠራተኛ ገንዘብ በጥሬም ሆነ
   በዓይነት መቀበል፤

በ) የሥራ ውልን በሚኒስቴሩ ሳያፀድቅ ሠራተኛን ለሥራ ማሰማራት

ተ) በሥራ ውሉ ከተመለከተው አገር ውጭ ሠራተኛን ለሥራ መላክ፤

ቸ) በተሰጠው ፈቃድ ከተመለከተው የአገልግሎት ዓይነት፣ የሥራ ቦታ ወይም አገር
   ውጭ መሥራት፤

ኀ) ሠራተኛን በፀደቀው የሥራ ውል ከተመለከተው አሠሪ ውጭ ለሌላ አሠሪ ማስተላለፍ፤

ነ) በዚህ አዋጅ፣ በሌላ ሕግ ወይም በፍርድ ቤት ውሳኔ በውጭ አገር ሥራ ስምሪት
   እንዳይሰማራ የተከለከለ ሰው በኤጀንሲው ሥራ ውስጥ እንዲሳተፍ ማድረግ፤

ኘ) ሠራተኛን ለመመልመልና ለሥራ ለማሰማራት ሲባል የተሳሳተ መረጃ
   ወይም ሰነድ መስጠት ወይም ማስታወቂያ ማውጣት፤

አ) የፀደቀውን የሥራ ውል ሚኒስቴሩን ሳያሳውቅና ሳያፀድቅ በሌላ መተካት ወይም መቀየር፤

ከ) ሕጋዊ የጉዞ ሰነዶችንና ሌሎች መረጃዎችን ሠራተኛ ወደ ሥራ
   ከመሰማራቱ በፊትም ሆነ በኋላ በማናቸውም ምክንያት መያዝ ወይም መከልከል፤

ኸ) የሠራተኛ የጉዞ ሰነድን ሆን ብሎ ማሳሳት ወይም መቀየር፤

ወ) ሠራተኛን በማታለል ወይም በማስገደድ ባለመብት የሆነበትን ጥቅሞች እንዲተው ማድረግ፡፡

፵፫. አቤቱታ ስለማቅረብ

፩/ ማንኛውም ተጎጂ ሠራተኛ ወይም የተጎጂው ሠራተኛ ተወካይ ይህን አዋጅ እና በአዋጁ መሠረት የወጣ ደንብ፣ መመሪያ ወይም ሌላ ተዛማጅነት ያለው ሕግ በኤጀንሲው ተጥሷል በሚል ለሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ላለው ባለሥልጣን አቤቱታ በጽሁፍ ወይም በቃል ማቅረብ ይችላል፡፡

፪/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት አቤቱታው የቀረበው በቃል ከሆነ የሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን ኦፊሰር አቤቱታውን በወረቀት ላይ በማስፈር አቤቱታ አቅራቢው እንዲፈርም ማድረግ አለበት፡፡

፫/ ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን በራሱ ተነሳሽነት ወይም በሌላ አካል የሚቀርብለትን በዚህ አዋጅ የተመለከተውን የሕግ ጥሰት የሚመለከት ሪፖርት መሠረት በማድረግ ጉዳዩ እንዲታይ ሊያደርግ ይችላል፡፡

፵፬. የአቤቱታ ይዘት

በዚህ አዋጅ በአንቀጽ ፵፫ መሠረት የሚቀርብ አቤቱታ ሌሎች ተጨማሪ ዝርዝር መግለጫዎች እንደተጠበቁ ሆኖ የሚከተሉትን መያዝ ይኖርበታል፦

፩/ የአቤቱታ አቅራቢ ስም እና አድራሻ፤

፪/ አቤቱታ የቀረበበት ኤጀንሲ ስም እና አድራሻ፤

፫/ የአቤቱታው ዓይነት፣ ፍሬ ጉዳይ እና ምክንያት፤

፬/ ለአቤቱታው ምክንያት የሆነው ድርጊት የተፈፀመበት ጊዜና ቦታ፤

፭/ በአቤቱታው የተጠየቀ ገንዘብ ካለ መጠኑ፤

፮/ የተጠየቀው መፍትሔ፤

፯/ ሌሎች አግባብነት ያላቸው ደጋፊ ማስረጃዎች፡፡

፵፭. አቤቱታ ስለመስማት

፩/ ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን በዚህ አዋጅ በአንቀጽ ፵፫ እና ፵፬ መሠረት አቤቱታ ሲቀርብ ፋይል በመክፈት አቤቱታውን የመመርመርና የመስማት ሂደት ይቀጥላል፡፡

፪/ ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን አቤቱታ እንደደረሰው የአቤቱታውን ቅጂና ደጋፊ ሰነዶች በማያያዝ አቤቱታ የቀረበበት ኤጀንሲ በአሥር የሥራ ቀናት ውስጥ መልሱን በጽሁፍ እንዲያቀርብ የመጥሪያ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡

፫/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፪) መሠረት በመጥሪያ ለደረሰው አቤቱታ ኤጀንሲው መልስ ካልሰጠ መልስ ሰጭ በሌለበት አቤቱታ የመስማት ሂደት ይቀጥላል፡፡

፬/ አቤቱታ አቅራቢው ያቀረበውን አቤቱታ በማናቸውም ምክንያት ቢያቋርጥ ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን ጉዳዩን በመመርመር ተገቢውን ውሳኔ ከመስጠት አያግደውም፡፡

፭/ ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን የቀረበለትን አቤቱታ በማጣራትና በመመርመር አቤቱታው በቀረበ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለጉዳዩ ውሳኔ ይሰጣል፡፡

፵፮. ጊዜያዊ እርምጃ ስለመውሰድ

ሚኒስቴሩ፦

፩/ ይህን አዋጅ፣ አዋጁን መሠረት አድርጎ የወጣ ደንብ ወይም መመሪያ በመጣሱ ምክንያት የቀረበበትን አቤቱታ አጣርቶ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ በተጠሪው ኤጀንሲ በኩል የሚቀርብን የሥራ ውል አያፀድቅም፤

፪/ በመታየት ላይ ያለ ጉዳይ ውሳኔ እስከሚያገኝ ድረስ በሚከተሉት ምክንያቶች የኤጀንሲውን ፈቃድ አግዶ ያቆያል፦

ሀ) አቤቱታ የቀረበበት ኤጀንሲ በአካል እንዲቀርብ ወይም አስፈላጊውን ሰነድ
   እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ደርሶት ይህንኑ ካልፈፀመ፤

ለ) ኤጀንሲው ሥራውን ቢቀጥል በሚመለምላቸው ሠራተኞች ላይ የከፋ የመብት
   ጥሰት ወይም ብዝበዛ የሚያስከትል ወይም ከማንኛውም አገር ጋር ያለውን
   ግንኙነት የሚጎዳ ወይም የአገርን ጥቅም የሚፃረር ድርጊት ለመኖሩ አሳማኝ ከሆነ፤

ሐ) ይህን አዋጅ፣ አዋጁን መሠረት አድርጎ የወጣ ደንብ ወይም መመሪያ በተጠሪው
   ኤጀንሲ ስለመጣሱ የሚያስረዳ ማስረጃ ከቀረበ፡፡

፵፯. አስተዳደራዊ እርምጃ

፩/ ማንኛውም ኤጀንሲ በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፵፪ (፪) የተመለከተው ጥፋት መፈጸሙ ሲረጋገጥ፣

ሀ) ድርጊቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጸመ ከሆነ ለሦስት ወር፣

ለ) ድርጊቱ ለሁለተኛ ጊዜ የተፈጸመ ከሆነ ለስድስት ወር፣

ሐ) ድርጊቱ ለሦስተኛ ጊዜ የተፈጸመ ከሆነ ለአሥራ ሁለት ወር፣ ፈቃዱ ይታገዳል፡፡

፪/ ማንኛውም ኤጀንሲ በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፵፪ (፪) የተጠቀሰውን ጥፋት ለአራተኛ ጊዜ ወይም በአንቀጽ ፵፪ (፫) የተመለከተውን ማንኛውንም ጥፋት መፈፀሙ ሲረጋገጥ ፈቃዱ ይሰረዛል፡፡

፫/ በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፵፪ (፫) ከፊደል ተራ (ሐ) በስተቀር ከፊደል ተራ (ሀ) እስከ (ወ) ከተዘረዘሩት ጥፋቶች አንዱን መፈጸም ከአስተዳደራዊ እርምጃ በተጨማሪ እንደ ሁኔታው አግባብ ባለው የወንጀል ሕግ ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡

፵፰. የፈቃድ መታገድ ወይም መሰረዝ የሚያስከትለው ውጤት

፩/ ፈቃዱ የታገደበት ወይም የተሰረዘበት ኤጀንሲ ሥራና ሠራተኛ የማገናኘት ተግባሩን ያቆማል፡፡

፪/ በዚህ አዋጅ መሠረት ፈቃዱ የተሰረዘበት ኤጀንሲ እርምጃው በተወሰደ በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ፈቃዱን ለሚኒስቴሩ ይመልሳል፡፡

፫/ ሚኒስቴሩ በማናቸውም ምክንያት የኤጀንሲን ፈቃድ ሲሰርዝ ወይም ሲያግድ ይህንኑ ለሚመለከታቸው አካላትና ለሕብረተሰቡ አመቺ በሆነ መንገድ ያሳውቃል፡፡

፬/ አግባብ ያለው ባለሥልጣን በማናቸውም ምክንያት የኤጀንሲን ፈቃድ ሲያግድ ይህንኑ ለሚመለከታቸው አካላትና ለሕብረተሰቡ አመቺ በሆነ መንገድ ያሳውቃል፡፡

፭/ ፈቃድ የታገደበት ወይም የተሰረዘበት ኤጀንሲ የላካቸው ሠራተኞች ከሚያነሱት የመብት ጥያቄ ነፃ አያደርገውም፡፡

፵፱. የውሳኔው ይዘት

ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን በዚህ አዋጅ በአንቀጽ ፵፭(፭) መሠረት በጽሁፍ የሚሰጠው ውሳኔ ግልፅና አጭር ሆኖ የሚከተሉትን መያዝ ይኖርበታል፦

፩/ የጉዳዩን ፍሬ ነገር፤

፪/ የጉዳዩን ጭብጥ፤

፫/ ለጉዳዩ አግባብነት ያለው ሕግ፣ ደንብ ወይም መመሪያ፤

፬/ ምክንያቶቹ እና ማጠቃለያ፤

፭/ የተሰጠ ውሳ

፶. የአፈፃፀም ትዕዛዝ ስለመስጠት

፩/ ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን በዚህ አዋጅ በአንቀጽ ፵፭(፭) መሠረት የሰጠውን ውሳኔ ኤጀንሲው እንዲፈጽም የጽሁፍ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡

፪/ ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት የሰጠውን ትዕዛዝ አቤቱታ የቀረበበት ኤጀንሲ በ፲፭ ቀናት ውስጥ የመፈፀም ግዴታ አለበት፣

፶፩. የውሳኔ አፈፃፀም ቅደም ተከተል

በዚህ አዋጅ መሠረት የሠራተኛ ምልመላ ሥርዓት ጥሰት በመፈፀሙ በሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ባለው ባለሥልጣን ወይም የሥራ ክርክር ለማየት ሥልጣን በተሰጠው አካል የተወሰነን ውሳኔ በሚመለከት የተሰጠን የአፈፃፀም ትዕዛዝ ኤጀንሲው ካልፈፀመ ውሳኔው በሚከተለው ቅደም ተከተል ተፈፃሚ ይሆናል ፦

፩/ ኤጀንሲው ለሠራተኞች ዋስትና ማስከበሪያ በዝግ ሂሳብ በባንክ ባስቀመጠው ገንዘብ፤

፪/ ኤጀንሲው የግል ድርጅት ከሆነ በሚንቀሳቀስ የግል ንብረት ላይ ወይም ኤጀንሲው የንግድ ማኅበር ከሆነ በሚንቀሳቀስ የማኅበሩ ንብረት ላይ፤

፫/ ኤጀንሲው የግል ድርጅት ከሆነ በማይንቀሳቀስ የግል ንብረት ላይ ወይም ኤጀንሲው የንግድ ማኅበር ከሆነ በማይንቀሳቀስ የማኅበሩ ንብረት ላይ፡፡

ንዑስ ክፍል ሁለት

በአሠሪ፣ በኤጀንሲ ወኪል ወይም በሠራተኛ የሚፈፀም ጥፋትና የሚወሰድ ዕርምጃ

፶፪. አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የመወሰን ሥልጣን

ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን በአሠሪ፣ የኤጀንሲ ወኪል ወይም ሠራተኛ ይህን አዋጅ እና በአዋጁ መሠረት የወጣ ደንብና መመሪያ በመጣሱ ምክንያት የሚነሱ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የመስማትና የመወሰን ሥልጣን ይኖረዋል፡፡

፶፫. በአሠሪ ወይም በኤጀንሲ ወኪል ስለሚፈፀሙ ጥፋቶች

በአሠሪ ወይም በኤጀንሲ ወኪል ላይ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ የሚያበቁ ጥፋቶች የሚከተሉት ናቸው ፦

፩/ በገባው የሥራ ውል መሠረት ግዴታውን አለመወጣት፤

፪/ በውክልናው መሠረት ግዴታውን አለመወጣት፤

፫/ የሠራተኛን ሕጋዊ የጉዞ ሰነዶች በማናቸውም ምክንያት መያዝ ወይም እንዳያገኝ መከልከል፤

፬/ የሠራተኛን ደመወዝ ወይም ሠራተኛው ወደ አገር የሚልከውን ገንዘብ ያለበቂ ምክንያት መያዝ፤

፭/ በቸልተኝነት ሠራተኛው ላይ ከባድ ጉዳት፣ ህመም ወይም የሞት አደጋ ማድረስ፤

፮/ የሠራተኛውን ሰብዓዊ ክብርና ሞራል የሚነካ ድርጊት መፈጸም፤

፯/ በሠራተኛው ላይ ጾታዊ ጥቃት መፈጸም፤

፰/ ይህን አዋጅ፣ አዋጁን ለማስፈጸም የወጣ ደንብ ወይም መመሪያን መጣስ፡፡

፶፬. በአሠሪ ወይም በኤጀንሲ ወኪል ላይ የአቤቱታ አቀራረብና ውሳኔ አሰጣጥ

፩/ ተጎጂ ሠራተኛ ወይም ማንኛውም ሰው በአሠሪው ወይም በኤጀንሲ ወኪል ጥፋት ተፈጽሟል በሚል አቤቱታ በጽሁፍ ወይም በቃል ለሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ላለው ባለሥልጣን ማቅረብ ይችላል፣

፪/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት አቤቱታው የቀረበው በቃል ከሆነ የሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን ኦፊሰር አቤቱታውን በወረቀት ላይ በማስፈር አቤቱታ አቅራቢው እንዲፈርም ማድረግ አለበት፡፡

፫/ ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን በራሱ ተነሳሽነት ወይም በሌላ አካል የሚቀርብለትን በዚህ አዋጅ የተመለከተውን የሕግ ጥሰት የሚመለከት ሪፖርት መሠረት በማድረግ ጉዳዩ እንዲታይ ሊያደርግ ይችላል፡፡

፬/ አቤቱታ የቀረበበት አሠሪ ወይም የኤጀንሲ ወኪል ጉዳዩ ታይቶ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ ከኢትዮጵያ ሠራተኛ እንዳይቀጥር ወይም በውጭ አገር ሥራ ስምሪት እንዳይሳተፍ ለጊዜው በሚኒስቴሩ ሊታገድ ይችላል፡፡

፭/ ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን የቀረበለትን አቤቱታ በማጣራት እና በመመርመር አቤቱታው በቀረበ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ውሳኔ ይሰጣል፡፡

፶፭. የአቤቱታ ይዘት

በዚህ አዋጅ በአንቀጽ ፶፬ (፩) እና (፪) መሠረት የሚቀርብ ማንኛውም አቤቱታ የሚከተሉትን መረጃዎች መያዝ ይኖርበታል ፦

፩/ የአቤቱታ አቅራቢው ስም እና አድራሻ፤

፪/ አቤቱታ የቀረበበት አሠሪ ወይም የኤጀንሲ ወኪል ስም እና አድራሻ፤

፫/ የተፈጸመ ጥፋት ዓይነት፤

፬/ ጥፋቱ የተፈፀመበት ጊዜና ቦታ፤

፭/ ሌሎች ደጋፊ ማስረጃዎች፡፡

፶፮. ውሳኔው የሚያስከትለው ሕጋዊ ውጤት

አቤቱታ የቀረበበት አሠሪ ወይም የኤጀንሲ ወኪል ጥፋት መፈጸሙ በሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ባለው ባለሥልጣን ውሳኔ ከተረጋገጠ ፦

፩/ አሰሪው ከኢትዮጵያ ውስጥ ሠራተኛን ለመቅጠር አይፈቀድለትም፤

፪/ የኤጀንሲው ወኪል በኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት ተግባር ሊሳተፍ አይችልም፤

፫/ በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፶፫ መሠረት በተፈፀመው ጥፋት ምክንያት በሠራተኛው ላይ ለደረሰ ጉዳት አሠሪው ወይም የኤጀንሲው ወኪል ተመጣጣኝ ካሣ ይከፍላል፡፡

፶፯. በሠራተኛ ስለሚፈፀሙ የጥፋት ዓይነቶች

የሚከተሉት ጥፋቶች በሠራተኛ ላይ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ የሚያበቁ ናቸው ፦

፩/ በገባው የሥራ ውል መሠረት ግዴታውን አለመወጣት፤

፪/ በኢትዮጵያ ወይም በተቀባይ አገር ባሉ ሕጎች በወንጀል የሚያስቀጣ ድርጊት መፈፀም፤

፫/ የተቀባይ አገር እምነት፣ ባህል እና ልማድን የሚፃረር ድርጊት መፈፀም፤

፬/ አግባብ ባለው የመንግሥት አካል የሥራ ውሉ ከፀደቀ በኋላ ያለበቂ ምክንያት በሥራ ላይ ለመሰማራት ፈቃደኛ ሆኖ አለመገኘት፤

፭/ የአሠሪን ወይም አብሮ የሚሰራ ሠራተኛን ገንዘብ ወይም ንብረት ያለአግባብ መጠቀም፤

፮/ ከውጭ አገር ሥራ ስምሪት ጋር በተያያዘ የተሳሳተ መረጃ ማቅረብ፤

፯/ ያለበቂ ምክንያት የሥራ ውል ማቋረጥ፡፡

፶፰. ስለሚወሰድ ዕርምጃ

በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፶፯ የተመለከተውን ጥፋት የፈፀመ ማንኛውም ሠራተኛ አግባብ ባለው ሕግ

፩/ ጥፋቱን የፈፀመው ለመጀመሪያ ጊዜ ከሆነ ከውጭ አገር ሥራ ስምሪት ዕድል ለስድስት ወር ጊዜ ይታገዳል፤

፪/ ጥፋቱን የፈፀመው ለሁለተኛ ጊዜ ከሆነ ከውጭ አገር ሥራ ስምሪት ዕድል ለአንድ ዓመት ጊዜ ይታገዳል፤

፫/ ጥፋቱን የፈፀመው ለሦስተኛ ጊዜ ከሆነ ለውጭ አገር ሥራ ስምሪት ብቁ አይሆንም፡፡

፶፱. ለፍርድ ቤት አቤቱታ የማቅረብ መብት

፩/ ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን የዚህን አዋጅ ድንጋጌ ወይም በአዋጁ መሠረት የወጣ ደንብ ወይም መመሪያ በመተላለፍ በሚፈፀመው ጥፋት ላይ በሰጠው ውሳኔ ቅር የተሰኘ ወገን ውሳኔው በደረሰው በ፲፭ ቀናት ውስጥ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወይም በክልል ሥልጣን ለተሰጠው ፍርድ ቤት አቤቱታ ማቅረብ ይችላል፡፡

፪/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት በፍርድ ቤት ታይቶ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ይሆናል፡፡

ክፍል ስድስት

ስለማህበራዊ ደህንነት አገልግሎት

ንዑስ ክፍል አንድ

ስለዋስትና ገንዘብና ኢንሹራንስ

፷. ስለዋስትና ገንዘብ

፩/ ማንኛውም ኤጀንሲ ለሠራተኛው መብት እና ደህንነት ዋስትና ማስከበሪያ የሚውል $100,000(አንድ መቶ ሺህ የአሜሪካን ዶላር) ወይም ተመጣጣኙን የኢትዮጵያ ብር በዝግ ሂሳብ በባንክ ማስቀመጥ አለበት፡፡

፪/ ሚኒስቴሩ ካልፈቀደ በስተቀር በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት በዝግ ሂሳብ የተቀመጠውን ገንዘብ ጉዳዩ የሚመለከተው ባንክ በማናቸውም ሁኔታ መልቀቅ አይችልም፡፡

፫/ በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፷፱ (፩) ፊደል ተራ (ሀ) እና (ለ) የተመለከተውን ኤጀንሲው ካልፈጸመ ሚኒስቴሩ ተቀማጭ ከሆነው የዋስትና ገንዘብ ላይ ወጪ በማድረግ ለተፈለገው ዓላማያውላል፡፡

፬/ ተቀማጭ የሆነው የዋስትና ገንዘብ በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፶፩(፩) እና በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፫) መሠረት በጥቅም ላይ ከዋለ ኤጀንሲው ተቀናሽ የሆነውን የዋስትና ገንዘብ መጠን በ፲ የሥራ ቀናት ውስጥ መልሶ መተካት ይኖርበታል፡፡

፭/ ኤጀንሲው በማናቸውም ሁኔታ ሥራውን ሲያቆም ሚኒስቴሩ የዋስትናውን ገንዘብ የሚለቀው ከሠራተኛ መብትና ጥቅም ጋር የተያያዘ ጥያቄ ሥልጣን በተሰጠው አካል በመታየት ላይ ካልሆነ እና በኤጀንሲው አማካይነት ለሥራ ወደ ውጭ አገር የተላኩ ሠራተኞች በሙሉ የሥራ ውላቸው ከተቋረጠ ከ፮ ወር በኋላ ነው፡፡

፷፩. የውጭ አሠሪዎች ዋስትና ፈንድ

፩/ በሚኒስቴሩ አማካኝነት ሠራተኛን የሚቀጥር ማንኛውም የውጭ አገር መንግሥታዊ ድርጅትም ሆነ ቀጥታ ቅጥር የተፈቀደለት ማንኛውም የውጭ አገር አሠሪ የሚቀጥራቸው ሠራተኞች በሥራ ውል መጣስ ምክንያት የሚያነሱትን የገንዘብ ክፍያ ጥያቄዎች መሸፈን እንዲቻል የውጭ አሠሪዎች የዋስትና ፈንድ በዚህ አዋጅ መሠረት ይቋቋማል፡፡

፪/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) የተመለከተው የውጭ አገር አሠሪ ለቀጠረው ለእያንዳንዱ ሠራተኛ ፶ የአሜሪካን ዶላር በዚሁ ድንጋጌ መሠረት ለተቋቋመው የውጭ አሠሪዎች ዋስትና ፈንድ መዋጮ ያደርጋል፡፡

፫/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት የተቋቋመውን የውጭ አሠሪዎች ዋስትና ፈንድ የሚያስተዳድረው ሚኒስቴሩ ይሆናል፡፡

፬/ የዋስትና ፈንዱ ጥቅም ላይ የሚውለው ፦

ሀ) በዋነኛነት በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) በተመለከተው መሠረት
   የሠራተኞችን የገንዘብ ክፍያ ጥያቄ ለመሸፈን፣ እና

ለ) ለትሬዠሪ ቦንድ መግዣና የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በሚያወጣው
   መመሪያ ለሚወሰኑ ሌሎች አትራፊና አስተማማኝ ኢንቨስትመንቶች፣ ብቻ ይሆናል፡፡

፭/ የዋስትና ፈንዱ በማናቸውም የዕዳ ክፍያ ምክንያት መያዣ ወይም ማቻቻያ ሊሆን አይችልም፡፡

፷፪. ስለኢንሹራንስ ሽፋን

፩/ ማንኛውም ለሥራ ወደ ውጭ አገር ለሚሄድ ሠራተኛ አሠሪው የሕይወትና የአካል ጉዳት ካሳ ኢንሹራንስ ሽፋን በአገር ውስጥ የመግባት ግዴታ አለበት፤ዝርዝሩ ሚኒስቴሩ በሚያወጣው መመሪያ ይወሰናል፡፡

፪/ ኤጀንሲ ወይም ሠራተኛ የኢንሹራንስ ፖሊሲ ሰነዱን ከሥራ ዉል ጋር አያይዞ ለሚኒስቴሩ ማቅረብ አለበት፡፡

ንዑስ ክፍል ሁለት

ለሠራተኞች ስለሚደረግ ድጋፍ

፷፫. ኃላፊነት

፩/ ሚኒስቴሩ እና እንደ አግባቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውጭ አገር ለሥራ የተሰማራ ሠራተኛ መብት፣ ደህንነትና ክብር መጠበቁን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

፪/ ማንኛውም ኤጀንሲ ለሥራ የላከውን ሠራተኛ አስመልክቶ አሠሪው በሥራ ውሉ መሠረት ያሉበትን ግዴታዎች እንዲያከብር የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡

፷፬. ስለድጋፍ አሰጣጥ

፩/ ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን ከውጭ አገር ሥራ ስምሪት ጋር በተያያዘ ከሠራተኛው ወይም ስለሠራተኛው ያገባኛል ከሚል ሰው የሚቀርብ የድጋፍ ጥያቄ በመቀበል ሊያስተናግድ ይችላል፡፡

፪/ ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት ስለቀረበው የድጋፍ ጥያቄ ወይም ሠራተኛው ስለገጠመው ችግር ኤጀንሲው ተገቢውን መፍትሄ በመስጠት ሠራተኛው ስላለበት ሁኔታ ሪፖርት እንዲያቀርብ ያዛል፡፡

፫/ በሠራተኛ ወይም ስለሠራተኛው ያገባኛል ከሚል ሰው ለሚቀርብ የድጋፍ ጥያቄ የሚመለከተው ኤጀንሲ ወይም አሠሪ ተገቢውን መፍትሄ ካልሰጠ ሚኒስቴሩ በዚህ አዋጅ መሠረት አስፈላጊውን አስተዳደራዊ እርምጃ ሊወስድ ይችላል፡፡

፬/ ዝርዝሩ በመመሪያ የሚወሰን ሆኖ ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን ከሚመለከ ታቸው አካላት ጋር በመተባበር በዚህ አዋጅ መሠረት ለሥራ ውጭ አገር ሄደው ወደ አገራቸው ለሚመለሱ ዜጎች የማቋቋሚያ ድጋፍ ያመቻቻል፡፡

፭/ ሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን ከውጭ አገር ሥራ ስምሪት ጋር በተያያዘ ተጎጂ ለሆነ ሠራተኛ ነፃ የሕግ ምክር አገልግሎት ይሰጣል፡፡

፷፭. በፈቃድ ወይም ለዕረፍት ወደ አገር የሚመጣ ሠራተኛን ስለመመዝገብ

በፈቃድ ወይም ለዕረፍት ወደ አገር የሚመጣና ይሰራበት ወደ ነበረው አሠሪ የሚመለስ ማንኛውም ሠራተኛ የሚከተሉትን ሰነዶች ለሚኒስቴሩ በማቅረብ መመዝገብ ይኖርበታል ፦

፩/ የፀና ፓስፖርት፤

፪/ ወደ ተቀባይ አገር መመለሻ ቪዛና የሥራ ፈቃድ፤

፫/ በሚኒስቴሩ የሚጠየቁ ሌሎች ማስረጃዎች፡፡

ንዑስ ክፍል ሦስት

ስለማስማማት እና ሠራተኛን ወደ አገር ስለመመለስ

፷፮. ስለማስማማት

ሚኒስቴሩ ወይም አግባብነት ያለው ባለሥልጣን ከውጭ አገር ሥራ ስምሪት ጋር በተያያዘ በሠራተኛ ፣በኤጀንሲ ወይም በአሠሪ ላይ የሚቀርብ አቤቱታን ተቀብሎ ሊያስማማ ይችላል፡፡

፷፯. ስለማስማማት ሂደት

፩/ ሚኒስቴሩ ወይም አግባብነት ያለው ባለሥልጣን አቤቱታን በተቀበለ በሦስት የሥራ ቀናት ውስጥ አቤቱታ ለቀረበበት አካል በማሳወቅ ሁለቱ ወገኖች ቀርበው ጉዳዩን በ፲፭ የሥራ ቀናት ውስጥ በስምምነት እንዲጨርሱ ጥረት ያደርጋል፡፡

፪/ ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮች በሁለቱ ወገኖች ላይ አስገዳጅነትና ተፈፃሚነት ይኖራቸዋል፡፡

፫/ የማስማማቱ ጥረት ካልተሳካ አቤቱታአቅራቢው ጉዳዩን ለሚኒስቴሩ ወይም አግባብ ላለው ባለሥልጣን የአቤቱታ መወሰኛ ሥራ ክፍል ማቅረብ ይችላል፡፡

፷፰. አስተዳደራዊ እርምጃ

አቤቱታ የቀረበበት ኤጀንሲ በቂ ባልሆነ ምክንያት፦

፩/ ለማስማማት በተያዘው ቀጠሮ ቀን ያልቀረበ እንደሆነ፣ ወይም

፪/ የተደረሰበትን ስምምነት ተግባራዊ ያላደረገ እንደሆነ፣ ይህንኑ እስኪፈጽም ድረስ በኤጀንሲው በኩል የሚቀርብ የሥራ ውልን ሚኒስቴሩ አያፀድቅም፡፡

፰፱. ሠራተኛን ወደ አገር ስለመመለስ

፩/ ማንኛውም ኤጀንሲ የሚከተሉት ግዴታዎች ይኖሩበታል ፦

ሀ) የሥራ ውል እንደተቋረጠ የአየር ትራንስፖ ርት ወጪ በመሸፈን
   ሠራተኛውንና የግል ንብረቶቹን ወደ አገሩ የመመለስ፤

ለ) ሠራተኛው ከባድ የአካል ጉዳት ሲደርስበት ወይም ሲሞት ጉዳት
   የደረሰበትን ሠራተኛ ወይም አስከሬን የሚቆይበት በቂ ምክንያት ከሌለ
   በስተቀር ከግል ንብረቶቹ ጋር የአየር ትራንስፖርት ወጪ በመሸፈን ሠራተኛው
   ስለደረሰበት ጉዳት ወይም ሞት ከሚገልጽ ሕጋዊ የህክምና ማስረጃ ጋር በማያያዝ
   በ፲፭ ቀናት ውስጥ ወደ አገሩ የመመለስ እና ተያያዥነት ያላቸው ሌሎች ወጪዎችን የመሸፈን፤

ሐ) የሥራ ላይ ጉዳት የደረሰበት ሠራተኛ ወደአገር ሲመለስ አስፈላጊ ገንዘብ ወጪ
   በማድረግ ሕክምና እንዲያገኝ የማድረግ፡፡

፪/ ሠራተኛው የሥራ ውሉን ያለበቂ ምክንያት ካቋረጠ ኤጀንሲው ሠራተኛውን ወደአገሩ በመመለስ ያወጣውን ወጪ ሊጠይቅ ይችላል፡፡

ክፍል ሰባት

ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

፸. አንድ ወኪል ከምን ያህል ኤጀንሲዎች እና አንድ ኤጄንሲ ከምን ያህል ወኪሎች ጋር መሥራት እንደሚችል ስለመወሰን

በተቀባይ አገር ሥራና ሠራተኛ ለማገናኘት የሚያስችል ፈቃድ ያለው ወኪል በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ከምን ያህል ኤጀንሲዎች ጋር ወኪል ሆኖ መሥራት እንደሚችል እንዲሁም ፈቃድ ያለው ኤጄንሲ በተቀባይ አገር ፈቃድ ካለው ከምን ያህል ወኪል ጋር መሥራት እንደሚችል ሚኒስቴሩ በመመሪያ ይወስናል፡፡

፸፩. ስለ ሥራ ክርክር አፈታት

በሠራተኛ እና በአሠሪ ወይም በኤጀንሲ መካከል ካለው የሥራ ግንኙነት በመነጨ የሚነሳ ማናቸውም የመብትና የጥቅም ክርክር ጉዳይ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ መሠረት በተቋቋመ የሥራ ክርክር ችሎት ይታያል፡፡

፸፪. የማስረዳት ግዴታ

በዚህ አዋጅ መሠረት ለሥራ ወደ ውጭ አገር የሚሄድ ሠራተኛ በሥራ ሁኔታዎች ላይ የሚያቀርበውን ክስ ወይም አቤቱታ ኤጀንሲው ወይም አሠሪው ከተቃወመ ክሱ ወይም አቤቱታው ሊደገፍ እንደማይገባ የማስረዳት ግዴታ የሚወድቀው በኤጀንሲው ወይም በአሠሪው ላይ ይሆናል፡፡

፸፫. ስለ ይርጋ

በዚህ አዋጅ መሠረት በአሠሪ፣ በኤጀንሲ፣ በኤጀንሲ ወኪል ወይም በሠራተኛ በሚፈፀም ጥፋት ምክንያት የሚቀርብ ማንኛውም አስተዳደራዊ አቤቱታ ጥፋቱ ከተፈፀመበት ወይም ጥፋቱ መፈፀሙ ከታወቀበት ቀን አንስቶ እስከ ሦስት ዓመት ድረስ ለሚኒስቴሩ ወይም አግባብነት ያለው ባለሥልጣን ካልቀረበ በይርጋ ይታገዳል፡፡

፸፬. ክልከላ

፩/ ማንኛውም ሰው ሠራተኛን ገንዘብ በማስከፈል የውጭ አገር ሥራና ሠራተኛ የማገናኘት ተግባር ማከናወን የተከለከለ ነው፡፡

፪/ ሚኒስቴሩ ለሥራ ወደ ውጭ አገር የሚሄዱ ዜጎች የሚሄዱበት አገር በጦርነት ቀጠና፣ በተፈጥሮ አደጋ ወይም በበሽታና በመሳሰሉት ምክንያቶች ለዜጎች ደህንነት አስጊ መሆኑን ካመነ ለሥራ ተቀጥረው እንዳይሄዱ ሊከለክል ይችላል፡፡

፸፭. ደንብና መመሪያ የማውጣት ሥልጣን

፩/ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለዚህ አዋጅ አፈፃፀም የሚያስፈልገውን ደንብ ሊያወጣ ይችላል፡፡

፪/ ሚኒስቴሩ ለዚህ አዋጅና በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) መሠረት የወጣውን ደንብ ለማስፈፀም መመሪያ ሊያወጣ ይችላል፡፡

፸፮. የመተባበር ግዴታ

ማንኛውም ሰው ለዚህ አዋጅ አፈፃፀም የመተባበር ግዴታ አለበት፡፡

፸፯. የተሻሩና ተፈፃሚ የማይሆኑ ሕጎች

፩/ ስለ ሥራና ሠራተኛ ማገናኘት አገልግሎት የወጣ አዋጅ ቁጥር ፮፻፴፪/፪ሺ፩ ተሽሯል፡፡

፪/ ይህን አዋጅ የሚቃረን ማንኛውም ሕግ፣ ደንብ፣ መመሪያ ወይም የአሠራር ልምድ በዚህ አዋጅ በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ተፈፃሚ አይሆንም፡፡

፫/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) የተደነገገው ቢኖርም፣ በአዋጅ ቁጥር ፮፻፴፪/፪ሺ፩ መሠረት የወጡ ደንቦችና መመሪያዎች ከዚህ አዋጅ ጋር እስካልተቃረኑ ድረስ በዚህ አዋጅ መሠረት በሚወጡ ደንቦችና መመሪያዎች እስከሚተኩ ድረስ ተፈፃሚነታቸው ይቀጥላል፡፡

፸፰. የመሸጋገሪያ ድንጋጌ

፩/ ለሥራ ወደ ውጭ አገር የተላከን ሠራተኛ በሚመለከት ይህ አዋጅ ከመፅናቱ በፊት በማናቸውም የሥራ ክርክር ሰሚ አካል ዘንድ በመታየት ላይ ያለ የሥራ ክርክር በተጀመረበት ሕግና ሥርዓት መሠረት ፍፃሜ ያገኛል፡፡

፪/ በአዋጅ ቁጥር ፮፻፴፪/፪ሺ፩ መሠረት ሠራተኛን በውጭ አገር ለሥራ ለማሰማራት ፈቃድ ተሰጥቶት የነበረ ማንኛውም ኤጀንሲ ሥራውን መቀጠል የሚፈልግ ከሆነ ይህ አዋጅ ከፀናበት ቀን ጀምሮ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ አዲስ ፈቃድ ማውጣት አለበት፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ አዲስ ፈቃድ ሳያወጣ ቢቀር ቀድሞ ተሰጥቶት የነበረው ፈቃድ ዋጋ አልባ ይሆናል፡፡

፫/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፪) መሠረት የተደነገገው ቢኖርም ፈቃዱ የተሰረዘበት ኤጀንሲ ለሥራ ወደ ውጭ አገር የላካቸው ሠራተኞች ከሚያነሱት ማናቸውም የመብት ጥያቄ ነፃ አያደርገውም፡፡

፬/ በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፸፯ (፩) የተደነገገው ቢኖርም የፀና ፈቃድ ላለው ማንኛውም የአገር ውስጥ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ እና በሀገር ውስጥ አዲስ ፈቃድ ለሚጠይቅ ሰው አግባብ ያለው ሌላ ሕግ እስኪወጣ ድረስ አዋጅ ቁጥር ፮፻፴፪/፪ሺ፩ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡

፸፱. አዋጁ የሚፀናበት ጊዜ

ይህ አዋጅ በፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የፀና ይሆናል፡፡

አዲስ አበባ የካቲት ፲፩ ቀን ፪ሺ፰ ዓ.ም

ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት